+251111265211 info@amharasc.org

News

ምርጫው ፍትህዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ውክልና የሚያረጋግጥ መሆን አለበት::

ምርጫ ዜጎች የአንድ ሀገር አካል መሆናቸው የሚገለጥበት አንዱ እና ዋነኛው ፖለቲካዊ ሂደት ነው፡፡ በሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) በአለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶቸ ቃልኪዳን (International Covenant on Civil & Political Rights) እንዲሁም በአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብት ቻርተር (African Charter on Human & Peoples Rights) እንደተደነገገው በአንድ ሀገር ውስጥ በምርጫ በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት መሳተፍ መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ነው፡፡ ስለሆነም ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በማንነታቸው የተነሳ በተለይ በተመራጭነት እንዳይሳተፉ ማድረግ ወይም የሚሳተፉበት ሁኔታ እንዲኖር አለማድረግ ወይም አለማመቻቸት መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ይህ አይነቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸመም በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ግዴታ እና ሃላፊነት አለባቸው፡፡
እንደሚታወቀዉ ከደርግ መውደቅ ማግስት በየአምስት አመቱ የይስሙላ ቢሆኑም ከእነችግራቸው ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች ከተፈጸሙት ጥፋቶች መካከል በብሔራቸው ከተሰየሙ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ዜጎች ስርዓታዊ በሆነ መልኩ በተመራጭነት እንዳይሳተፉ መደረጉ ነው፡፡ ለዚህ ትልቁ ማሳያ ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ የክልላዊ አስተዳደሮች ምክር ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ክልሉ በተሰየመው ብሔር ተወላጆች የተያዙ መሆኑ እና ምክር ቤቶቹ የክልሉን ነዋሪዎች ብዝሃነት የማያሳይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሁኔታ የዕኩልነት እና የኢ-አድሏዊነት መብትን (the right to equality & non-discrimination) የሚቃረን እና መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚያሳይ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተለይም በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠረው የአማራ ተወላጅ የዚህ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲነገር እንደነበረው መጪው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ቅቡልነት (legitimacy) ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን ግን በቅድሚያ በብሔራቸው ከተሰየመ ክልል ውጭ የሚኖሩ ዜጎች በምርጫው በመራጭነት ብቻ ሳይሆን በተመራጭነትም የሚሳተፉበት አስቻይ ሁኔታ ከወዲሁ ማመቻቸት እና በተግባራም እውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባልሆነበት መልኩ ሌሎች ሁኔታዎች ቢሟሉም እንኳን ምርጫው ፍትሃዊ እና ቅቡልነት ያለው ምርጫ ነው ለማለት አያስችልም፡፡ ከእኩልነት እና ከኢ-አድሏዊነት መርህ ጋር በሚቃረን መልኩ በምርጫው በማንነታቸው የተነሳ በተመራጭነት የማይሳተፉ ዜጎች እስከአሉ ድረስ የምርጫ ሂደት በማንኛውም መለኪያ ፍትሃዊ እና ቅቡልነት ያለው ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም የአማራ ተወላጆችን ጨምሮ በብሔራቸው ከተሰየሙ ክልሎች ውጭ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊን በመጪው ምርጫ በመራጭነት ብቻ ሳይሆን በተመረጭነት የሚሳተፉበት አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስተዳደር ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈላጊውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በተለይም ገዥው የብልጽግና ፓርቲ በፕሮግራሙ ላይ ትክክለኛ ሕብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም እውን እንዲሆን እሰራለሁ እንዳለው ሁሉ፤ በተጨባጭ የክልል ምክር ቤቶች እውነተኛ ሕብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምን የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ በሚወዳደርባቸው ክልሎች ክልሎቹ ከተሰየሙበት ብሔር ተወላጅ ያልሆኑ የክልሉ ነዋሪ የሆኑ አባላቶቹ በተመራጭነት እንዲወዳደሩ የማድረግ የተለዬ ሃላፊነት እና ግዴታ አለብት፡፡

ፈጣሪ ሀገራችንን እና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!!!
የምሁራን መማክርት ጉባዔ
ቀን 17/06/2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

February 25, 2021 News

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *